Latest blog posts

የቀድሞ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታ፣ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆንና የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን መርተዋል በሚል ተጠርጥረው ብቻቸውን በተከሰሱበት ክስ ላይ፣ ዓቃቤ ሕግ ከሐምሌ 14 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ የሙያ ምስክሮችን ማሰማት ጀመረ፡፡ 

በአቶ መላኩ ፈንታ ላይ ብቻ በክስ መዝገብ ቁጥር 141354 በሁለተኛ ክስነት የቀረበባቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ የሚያስረዱ የሙያ ምስክሮችን በመስማት ላይ የሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ሲሆን፣ ሐምሌ 14 ቀን 2006 ዓ.ም. ከሰዓት በፊት አንድ የዓቃቤ ሕግ ምስክርን ሰምቶ አጠናቋል፡፡ 

ምስክሩ የሚሰጡት የምስክርነት ቃል ያማማቶ ኢትዮጵያ የተባለ አስመጪ ድርጅት ባለቤት አቶ አህመድ አብዱላሂ፣ ከ1996 እስከ 2001 ዓ.ም. ድረስ የተጨማሪ እሴት ታክስና የንግድ ሥራ ገቢ ግብር ኦዲት ተደርጎ ከተገኘ ከ48.4 ሚሊዮን ብር ጋር በተያያዘ ክስ ላይ ነው፡፡ 

ነጋዴው የተጠቀሰውን ገንዘብ እንዲከፍሉ የውሳኔ ማስታወቂያ ሲደርሳቸው፣ ልደታ ክፍለ ከተማ ለሚገኘው የአነስተኛ ግብር ከፋዮች ጽሕፈት ቤት አቤቱታ ያቀርባሉ፡፡ ያቀረቡትን አቤቱታ ያጣራው አቤቱታ አጣሪ ኮሚቴ የግብር ግምቱ ትክክል መሆኑን ያፀድቃል፡፡ ነጋዴው የተወሰነባቸውን ግብር 50 በመቶ በማስያዝ ለግብር ይግባኝ ጉባዔ ማቅረብ ሲገባቸው ቅሬታቸውን ለአቶ መላኩ ፈንታ ማቅረባቸውን፣ አቶ መላኩም በአዋጁ መሠረት ግለሰቡን ወደ ይግባኝ ጉባዔው መላክ ሲገባቸው፣ አዋጁን በተፃረረ መልኩ የነጋዴውን አቤቱታ ተቀብለው፣ በድጋሚ እንዲታይላቸው በማድረግ ቀድሞ ተወስኖባቸው የነበረው 48.4 ሚሊዮን ብር ወደ 34 ሚሊዮን ብር ዝቅ እንዲል ማስደረጋቸውን በሚመለከት፣ የሙያ ምስክሮቹ እንዲያስረዱለት የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ጭብጥ አስይዞ ምስክሩ መደመጥ ጀመሩ፡፡ 

የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ምስክሩ ለምን እንደመጡ ለፍርድ ቤቱ እንዲያስረዱለት ያቀረበላቸውን ጥያቄ ተከትሎ ምስክሩ እንደተናገሩት፣ ሙደሲር ጁሀርና አሚናት የተባሉ ባልና ሚስት፣ የቁርጥ ግብር ከፋዮች (የቀን ገቢያቸው ታስቦ ግብር የሚከፍሉ) በመሆናቸው፣ የእነሱ ግብር ሲታሰብ የያማማቶ ማኅተም ያረፈበትና ከ700 ሺሕ ብር በላይ ግዢ የተፈጸመበት ደረሰኝ መገኘቱን ምስክሩ አስረድተዋል፡፡ በደረሰኙ (ፋክቱር) ላይ ሙሉ ስምና የድርጅቱ አድራሻ በአግባቡ ተጽፎ መሰጠት ሲገባው ስም ብቻ ያረፈበት ፋክቱር በመሆኑ፣ የያማማቶ ኢትዮጵያ የሒሳብ መዝገብ በገቢዎችና ጉምሩክ የኢንተለጀንስ ሠራተኞች ወደ ኦዲት ቢሮ እንዲመጣ መደረጉን ምስክሩ አክለዋል፡፡ ከ1996 እስከ 2001 ዓ.ም. ድረስ ያለውን የንግድ ትርፍ ግብርና የተጨማሪ እሴት ታክስ ምርመራ ሲደረግ፣ ያማማቶ ኢትዮጵያ ያልከፈለው በድምሩ ከ48.4 ሚሊዮን ብር በላይ ግብር መገኘቱንና እንዲከፍል እንደተወሰነበት አስረድተዋል፡፡ 

የሉዲና የተለያዩ ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች አስመጪ የሆነው ያማማቶ ኢትዮጵያ በባለሥልጣኑ በተፈቀደለትና በተሰጠው ደረሰኝ መሸጥ እንደነበረበት የገለጹት ምስክሩ፣ እሱ ግን ያለደረሰኝ ሲሸጥ እንደነበር መስክረዋል፡፡ የትርፍ ገቢ ግብር ከ32 ሚሊዮን ብር በላይ፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ ደግሞ ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲከፍል ግምት መወሰናቸውንና ለልደታ ክፍለ ከተማ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ጽሕፈት ቤት ማስተላለፋቸውን ምስክሩ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ያማማቶ ኢትዮጵያ ለጽሕፈት ቤቱ አቤቱታ ቢያቀርብም ውሳኔው እንደፀናበትም መስማታቸውን ምስክሩ አክለዋል፡፡ 

ኮሚቴ ተቋቁሞ ውሳኔው በድጋሚ እንዲታይ በስብሰባና በባለሥልጣኑ የኦዲት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በላቸው በየነና የታክስ አማካሪው አቶ ማሞ አብዱ በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብላቸውም፣ ምስክሩ የኦዲት ቡድኑ አለመስማማቱን አስረድተዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ ‹‹አዘዋል›› በማለት በቃል በመግለጽ አቶ በላቸውና አቶ ማሞ ጫና እንዳደረጉባቸውም ገልጸዋል፡፡ በኋላ በ1996 ዓ.ም. አቶ ሙደሲርና ወይዘሮ አሚና ግብይት የፈጸሙባቸው ፋክቱሮች በፎረንሲክ እንዲመረመሩ ተደርጎ፣ ‹‹ፋክቱሮቹ የያማማቶ ኢትዮጵያ አይደሉም›› በመባሉ፣ የአንድ ዓመት የ1996 ዓ.ም. ብቻ ሒሳብ ተቀንሶ ከ48 ሚሊዮን ብር ወደ 34 ሚሊዮን ብር ዝቅ ማለቱን አስረድተዋል፡፡ 

ጠበቆች በመስቀለኛ ለምስክሩ ባቀረቧቸው ጥያቄዎች፣ ፋክቱሮቹ በፎረንሲክ የተመረመሩት የመጀመሪያ ኦዲት ተደርጎ የግምት ውሳኔ ከመናገሩ በፊት ወይም በኋላ መሆኑን እንዲያስረዱ ጠይቀዋቸው፣ የመጀመሪያ ኦዲት ሠርተው ውሳኔ ካስተላለፉ በኋላ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ኮሚቴ የተቋቋመው ለዚህ ብቻ ነው ወይ ተብለው ሲጠየቁም እርግጠኛ እንዳልሆኑና ስለኮሚቴው የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ በመስቀለኛ ጥያቄና ምላሽ ወቅት ምስክሩ ድርጅቱ ፋክቱሩ የራሱ ሰነድ እንደሆነ ማመልከቱን ለእሳቸው ቢሮ ግን አለመግለጹን፣ አቤቱታ አጣሪው በጽሑፍ ጠይቆ በጽሑፍ እንደመለሰ፣ አራት ፋክቱር አግኝተው እንደመረመሩና ውጤቱም የያማማቶ አለመሆኑን እንዳረጋገጠ ገልጸዋል፡፡ 

ኮሚቴው ያቀረበውን ውሳኔ ለዋና ዳይሬክተሩ ማቅረብ መቻል አለመቻሉን የተጠየቁት ምስክሩ፣ ኮሚቴውን ያቋቋሙት ዋና ዳይሬክተሩ በመሆናቸው በግብር አዋጁ መሠረት ለእሳቸው ማቅረብ እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡ አቶ መላኩ ፈንታ ግብሩ ከተወሰነ በኋላ ያዘዙት ወይም የላኩት ደብዳቤ ስለመኖሩ ተጠይቀው፣ ምስክሩ ‹‹የለም›› ብለዋል፡፡ 

ግብሩ እንዴት እንደተሰበሰበ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ የገለጹት ምስክሩ፣ ስለአቶ መላኩም ‹‹የማውቀው ነገር የለም›› ብለዋል፡፡ የኦዲት ሥራ አጠራጣሪ ነገሮችን አጣርቶ ማቅረብ ወይም መሥራት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ የፍርድ ቤቱ ሦስቱም ዳኞች የማጣሪያ ጥያቄ ለምስክሩ በማቅረብ፣ ግልጽ ያልሆኑ የምስክሩ ምላሾችን አጥርተዋል፡፡ የሐምሌ 14 ቀን የግማሽ ቀን ምስክርነትም በዚህ አጠናቀዋል፡፡ 


Editors Pick

Arbitration Blog
The case between Salini Costruttori S.p.A v. AAWSA, ICC Case 10623, is very interesting. What makes the case appealing is Ethiopian Supreme Court’s interference in the proceeding and the consequent ex...
5555 hits
Legislative Drafting Blog
Modernization relies on law as the means of transformation. In these great processes of transformation, day after day, many more demands for new legislation have been proposed as a reaction to differe...
8534 hits
Arbitration Blog
1. Introduction   Arbitration has been a prevalent method of dispute settlement, in various countries of the world of today and yesterday. Arbitration is defined in the Black’s Law Dictionary as “a me...
8527 hits
Criminal Law Blog
Introduction Like many other countries around the globe, Ethiopia has embraced ICTs and ICT based services as key enabler for social and economic development in the country. Various efforts are also u...
23478 hits

Top Blog Posts

About the Law Blog
  መግቢያ የአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ቀደም ሲል አውጥቶት የነበረውና የተከራየን ሰው ማስወጣት (በርግጥ ደንቡ ይህን ድርጊት አልከለከለም) እና የኪራይ ዋጋን መጨመር ለማገድ የወጣውን የደንብ ቁጥር 122/13 ማራዘሙን በድጋሜ አስታዉቋል፡፡ ይህ ደንብ የቤት አከራዮች ያከራዬት ቤት ላይ ዋጋ እንዳንይጨምሩ ...
Taxation Blog
It is perplexing for me, as a tax lawyer having worked for close to 10 years on Ethiopian tax laws, to see how the investment and finance community in Ethiopia is not worrying enough about the tax on ...
Succession Law Blog
መግቢያ ማንኛውም ሰው አንድ የፍርድ ውሰኔ ሊያገኝ የሚገባ ጉዳይ ያለው እንደሆነ ጉዳዩን ለማየት በሕግ ሥልጣን ለተሰጠው አካል ሊያቀርብ ሚችልበት የጊዜ ገደብ በልዩ ልዩ የሕግ ድንጋጌዎች ላይ ተመልክቶ ይገኛል፡፡ ይህን መሰል የጊዜ ገደብ በሕግ አጠራር ይርጋ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ትርጓሜውም በሕግ በተቀመጠው የጊዜ ገደ...
Succession Law Blog
መግቢያ የውርስ ህግ ክፍል በሆነው የፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 826 ላይ እንደተመላከተው አንድ ሰው የሞተ አንደሆነ በሞተበት ጊዜ ዋናው መኖሪያው በሆነበት ስፍራ የዚህ የሟች የውርስ ሀብት ይከፈታል፡፡ የሟች ውርስ ሟች በሞተበት ቅጽበት የሚከፈት ቢሆንም የሟች የውርስ ሀብት እስከሚጣራ ድረስ የሟች ንብረት እንደ አንድ የ...