ኮሚሽኑ ረቂቅ ሕጉ ለጉምሩክ ኃላፊ የሚሰጠው ክስ እንዲመሠረት የማድረግ ሥልጣን እንዲሰረዝ ወይም እንዲጠብ በተጨማሪነት ጠይቋል፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት ለፓርላማው ቀርቦ ፓርላማው ለራሱ የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮችና የሕግና ፍትሕ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች ለዝርዝር ዕይታ መርቶት ነበር፡፡ የፀረ ሙስና ኮሚሽን የሥራ ኃላፊዎችም ረቂቅ ሕጉ ላይ ያሉ ድንጋጌዎችን የተቃወሙትና ማስተካከያ ሊደረግባቸው ወይም ሊሰረዙ ይገባሉ ያሏቸውን አንቀጾች ያነሱት፣ የበጀትና የፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በረቂቁ ላይ ባለፈው ሰኞ ባዘጋጀው የባለድርሻ አካላት ውይይት ላይ ነው፡፡
የጉምሩክ ረቂቅ አዋጅ በምዕራፍ ሁለት ድንጋጌው የጉምሩክ ወንጀሎችና ቅጣቶች በሚል ርዕስ ሥር ማንኛውም የጉምሩክ ሹም ወይም የፌዴራል ፖሊስ አባል ወይም በባለሥልጣኑ ሥራ በመተባበር የተሳተፈ ሰው፣ የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት ወይም በሌላ ሰው መብት ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ ወይም በቸልተኝነት አገልግሎቶችን ያጓተተ፣ ዕቃዎች እንዲያዙ፣ ማጓጓዣዎች ከጉዟቸው እንዲስተጓጎሉ ያደረገ ወይም የመሳሰሉትን የፈጸመ ከሆነ ከሦስት ዓመት በማያንስና ከአሥር ዓመት በማይበልጥ እስራት እንደሚቀጣ ያስረዳል፡፡
የተሰጠውን ሹመት በግልጽ ተግባር ወይም በግድፈት ያላግባብ የተገለገለና ከተሰጠው ሥልጣን አልፎ የሠራ የጉምሩክ ወንጀል እንደሆነ ተቆጥሮ ከሦስት ዓመት በማያንስና ከአሥር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣ ይገልጻል፡፡
የጉምሩክ ሹም ወይም የፌዴራል ፖሊስ በጉምሩክ ሕጎች የተደነገገውን እንዳይፈጽም ወይም የተከለከለውን እንዲያደርግ መደለያ የሰጠ ወይም መደለያ እንዲሰጥ ወይም እንዲቀበል ያደረገ ማንኛውም ሰው ከሰባት ዓመት በማያንስና ከአሥር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራትና ከብር 50,000 በማያንስና ከ100,000 ብር በማይበልጥ መቀጮ እንደሚቀጣ በረቂቁ ተወስቷል፡፡
አቶ ገብሩ ገበየሁ የተባሉ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሥራ ኃላፊ ረቂቅ ሕጉ ላይ ባለፈው ሰኞ በፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ በተዘጋጀው ውይይት ላይ ተገኝተው፣ ፀረ ሙስና ኮሚሽን የረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 166 እና 167 ማለትም ከላይ የተዘረዘሩት የወንጀል ዓይነቶች የጉምሩክ ወንጀል ተብለው መቀመጣቸው ተገቢ አለመሆኑን በጽሑፍ ለሚመለከታቸው የሕጉ አመንጪ አካላት ማሳወቁን አስረድተዋል፡፡
ይሁን እንጂ አግባብ አይደለም በሚል በኮሚሽኑ አስተያየት የተሰጠባቸው ሐሳቦች ለፓርላማ በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ባለመካተታቸው የኮሚሽኑን ሥጋት በአካል ለማቅረብ መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
‹‹አስተያየታችን መሠረት ያደረገው የሙስና ወንጀልና የጉምሩክ ወንጀል መካከል ልዩነት አልተፈጠረም የሚል ነው፤›› ያሉት የሥራ ኃላፊው፣ በተጠቀሱት አንቀጾች የተቀመጡት ድርጊቶች የሙስና ወንጀሎች ናቸው ብለዋል፡፡ ‹‹አሁንም ቢሆን በሥልጣን ያላግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል ነው፡፡ በጉምሩክ ሕግ ውስጥ የጉምሩክ ወንጀል ተብሎ የሚታለፍ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡
ከላይ የተዘረዘሩት ወንጀሎች በሙስና ካልተያዙ የታክስ ሥርዓቱ ላይ ትልቅ አደጋ ነው የሚፈጥሩት ያሉት የሥራ ኃላፊው አቶ ገብሩ፣ በሌሎች የመንግሥት ተቋማት ሥር ያሉ የሥራ ኃላፊዎች ያላግባብ ሥልጣንን መገልገል በሚል በሙስና እየተጠየቁ፣ ይህንኑ ወንጀል የጉምሩክ ሠራተኞች ሲፈጽሙ በጉምሩክ ወንጀል የሚዳኙበት ሥርዓት መፍጠር አግባብነት እንደሌለው አብራርተዋል፡፡
‹‹እንደዚህ ዓይነት ሕግ በዜጎች መካከል ልዩነትን የሚፈጥር ነው፡፡ አንዱ በጉምሩክ ሕግ እንዲዳኝ ሌላው ደግሞ ጠንከር ባለው የሙስና ወንጀል የሚዳኝበትን ሁኔታ ይፈጥራል በማለት አግባብ እንደሌለው በመጠቆም የኮሚሽኑን አቋም ገልጸዋል፡፡
የፀረ ሙስና ኮሚሽን ተወካዩ በተጨማሪ ያነሱት ነጥብ ሙሉ በሙሉ ኮሚሽኑን የሚመለከት ባይሆንም እንደተቋም ግን የሚያገባው በመሆኑ የተሰጠ አስተያየት ነው፤›› ብለዋል፡፡ አስተያየቱ የሚያተኩረው በጉምሩክ ረቂቅ አዋጅ አንቀጽ 150 ላይ የሰፈረውንና ለጉምሩክ ኃላፊ ክስ ያለመመሥረት ሥልጣን የሚሰጠውን ረቂቅ ድንጋጌ ላይ ነው፡፡
በረቂቅ ድንጋጌው መሠረት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር የጉምሩክ ወንጀል ፈጽሟል የተባለ ሰው በዕድሜ መጃጀት ወይም በበሽታ ምክንያት ጉዳዩን በፍርድ ቤት መከታተል የማይቻል ከሆነ፣ ጉዳዩ በክስ ሒደቱ ውስጥ ቢያልፍ ብሔራዊ ጥቅምን ወይም ዓለም አቀፍ ግንኙነትን ይጎዳል ብሎ ካመነ ክሱ እንደማይመሠረት ሊያደርግ እንደሚችል ያስቀምጣል፡፡ በተጨማሪም የክሱ መመሥረት ተመጣጣኝና ሚዛናዊ ያልሆነ የጎንዮሽ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑ ከታመነበት ወይም ወንጀሉ ሥልጣን ላለው ፍርድ ቤት ሳይቀርብ በመቆየቱ አስፈላጊነቱን ያጣ ከሆነ፣ ዋና ዳይሬክተሩ ክስ እንዳይመሠረት ሊያደርግ እንደሚችል በረቂቁ ተመልክቷል፡፡
የኮሚሽኑ ተወካይ ‹‹ክስ እንደማይመሠረት ማድረግ የሚቻልባቸው ሁኔታዎች ሊኖሩ ቢችሉም፣ በጉምሩክ ረቂቅ አዋጅ ላይ የተቀመጡት ምክንያቶች ግን በጣም ልቅ ሆነዋል በመሆኑም ከተቻለ ቢሰረዙ ወይም የሚጠበብት ሁኔታ ቢፈጠር፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት የግልግል ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዮሐንስ ወልደገብርኤልም በዚህ ጉዳይ ላይ ሙያዊ አስተያየቶችን ሰጥተዋል፡፡ ‹‹በዕድሜ መጃጃት ማለት ምን ማለት ነው? 50 ዓመት ነው? 70 ዓመት ነው? በበሽታ ምክንያት ማለትስ ምን ማለት ነው? በሽታ ማለት ጉንፋን ነው? ወረርሽኝ ነው?›› በማለት ለዋና ዳይሬክተሩ የሚሰጠውን ክስ ያለመመሥረት መብት ለትርጉም ክፍት መሆን አስረድተዋል፡፡ ‹‹በዓቃቤ ሕግ ዓይን ስናየው በዚህ መሥፈርት መሠረት ማንኛውንም ክስ እንዳይመሠረት ማድረግ ይቻላል፤›› ብለዋል፡፡
በተነሱት ሐሳቦች ላይ ምላሽ እንዲሰጡ ዕድል ከተሰጣቸው መካከል ሕጉን በማመንጨት ድርሻ የነበረው የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የሕግ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዋሲሁን አባተ፣ የሙስና ወንጀሎችና የጉምሩክ ወንጀሎች አልተለዩም የሚለውን የፀረ ሙስና ኮሚሽን ሥጋት በተመለከተ በረቂቅ ሕጉ የጉምሩክ ወንጀል እንዲሆኑ የተደረበት ምክንያት ቅጣቱን ጠበቅ ለማድረግ ሲባል ነው ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ ሥጋቱ በተደጋጋሚ በመነሳቱ በድጋሚ ለማየት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ በረቂቅ ሕጉ ላይ የገቢዎችና ጉምሩክ ዋና ዳይሬክተር ክስ ያለመመሥረት የሚችልባቸውን ጉዳዮች በተመለከተ የተነሳውን የአግባብነት ጥያቄ በተመለከተ፣ ‹‹ክስ የማይመሠረትባቸውን ምክንያቶች እኛ ዝም ብለን አይደለም ያመጣነው፡፡ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ፖሊሲው ላይ የተቀመጡ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡
‹‹የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ፖሊሲው ላይ ክስ ላለመመሥረት በምክንያትነት የተዘረዘሩትን ነው በረቂቅ የጉምሩክ ሕጉ ላይ እንዲቀመጥ የተደረገው፤›› ያሉት አቶ ዋሲሁን፣ የወንጀል ፖሊሲውን የሚዘረዘርና የሚተነትነው በመዘጋጀት ላይ ባለው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ በመሆኑ፣ ሥነ ሥርዓቱ ሲሻሻልና ሲፀድቅ መጃጀት ማለት ምን ማለት ነው? በሽታ ማለት ምን ማለት ነው? የሚሉትና ሌሎቹ ምክንያቶቹም ይዘረዘራሉ በማለት መፍትሔውም በዚያ ወቅት እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ውይይቱን ያዘጋጀው የፓርላማው የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከውይይቱ ያገኛቸውን ሐሳቦች ጨምቆ ፓርላማው ሰኔ 30 ቀን 2006 ዓ.ም. ለእረፍት ከመበተኑ በፊት አዋጁ እንዲፀድቅ ለፓርላማው ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡