Latest Blog posts
Editors Pick
Latest documents
Education and Training Policy of Ethiopia - Amharic version - 2023 7210 Downloads - policies and strategies | 7.6 MB | |
The Normative Basis for Decision on the Merits in Commercial Arbitration - the Extent of Party Autonomy 187 Downloads - Arbitration Law | 635.59 KB | |
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የህግ ትርጉም የሰጠባቸው ውሣኔዎች ማውጫ ቅጽ 01-25 8541 Downloads - Federal Supreme Court Cassation Bench Decisions | 10.72 MB | |
ስለ ወንጀል ተጎጂዎች - የአዲስ እይታ አስፈላጊነት በረቂቁ የወንጀል ሕግ የሥነ-ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ ላይ FEATURED 370 Downloads - Criminal Law | 317.19 KB | |
Federal Supreme Court Cassation Decisions - Table of content Volume 1-25 10258 Downloads - Federal Supreme Court Cassation Bench Decisions | 6.57 MB |
- Details
- Category: Legal News - የሕግ ዜናዎች
በተመሳሳይ የወንጀል ጥርጣሬ የተለያየ ትዕዛዝ የተሰጠባቸው ጋዜጠኞችና ጦማርያን የፍርድ ቤት ውሎ
‹‹ከተደጋጋሚና አሰልቺ ‘አባል ነህ?’ ጥያቄ ውጪ ምንም አልተጠየቅንም›› ተጠርጣሪ ጋዜጠኞች
በህቡዕ በመደራጀት፣ ሥልጠና በመውሰድና በውጭ ከሚገኙ አሸባሪዎች ጋር በመገናኘት የአመፅ ወንጀል ለመፈጸም ሲቀሳቀሱ ነበሩ ተብለው የተጠረጠሩት ጋዜጠኞችና ጦማርያን ላይ ፍርድ ቤት የተለያዩ ትዕዛዞች ሰጠ፡፡
በቁጥጥር ሥር ከዋሉ 26 ቀናት ያስቆጠሩት ተጠርጣሪዎቹ ለሦስተኛ ጊዜ በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት ግንቦት 9 እና 10 ቀን 2006 ዓ.ም. ቀርበዋል፡፡ ግንቦት 9 ቀን 2006 ዓ.ም. የቀረቡት ተጠርጣሪ ጋዜጠኞች ተስፋለም ወልደየስ፣ አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስና ኤዶም ካሣዬ ሲሆኑ፣ ጦማርያኑ ደግሞ መምህር ዘላለም ክብረት፣ ናትናኤል ፈለቀና አጥናፍ ብርሃን ናቸው፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ከጠዋቱ አራት ሰዓት ላይ ፍርድ ቤት የደረሱ ሲሆን፣ እነሱ ከመድረሳቸው በፊት የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት ቀደም ብለው ፍርድ ቤቱ ቅጥር ግቢ በመድረስ፣ የተጠርጣሪዎቹን መምጣት ይጠባበቁ የነበሩ ቤተሰቦች፣ ጓደኞች፣ ጋዜጠኞች፣ የተለያዩ ኤምባሲዎች ዲፕሎማቶችና ሌሎችን ወደ አንድ ጥግ ተሰብስበው እንዲቆሙ አደረጉ፡፡
ሁለት ሌሎች ተጠርጣሪዎችን ተከትለው ወደ ችሎቱ የገቡት ኤዶም፣ ናትናኤልና አጥናፍ ናቸው፡፡ ናትናኤልና አጥናፍ ፊታቸውን ቅጭም እንዳደረ የታሰሩበትን ሰንሰለት እያዩና በታሰረ እጃቸው ሰላምታ በሚመስል መልኩ ወደ ጐን ወደ ሕዝቡ እያዩ ወደ ውስጥ ዘለቁ፡፡ ከእያንዳንዳቸው ሦስትና ሁለት ቤተሰብ እንዲገባ ተፈቅዶ ችሎቱ ሥራውን ጀመረ፡፡
ችሎቱን ከታደሙትና ከተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ የዕለቱን የምርመራ ሒደት ለመረዳት እንደተቻለው፣ የፌዴራል መርማሪ ቡድን ያካሄደውን የምርመራ ውጤት እንዲያስረዳ ፍርድ ቤቱ ጠይቆታል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በህቡዕ በመደራጀት በሕጋዊ መንገድ ሥልጣን የያዘውን መንግሥት በሕገወጥ ሁኔታ ለማስወገድ በማሰብ፣ በውጭ አገር ከሚገኙ አሸባሪዎች ጋር በመስማማት አገሪቱንና ሕዝቡን ለማተራመስ ገንዘብና ትዕዛዝ በመቀበል፣ ሥልጠና በመውሰድ፣ ብጥብጥ ለማስነሳትና ለመምራት፣ የሽብር ድርጊት ለመፈጸም መንቀሳቀሳቸውን የሚያሳይ ፍንጭ ማግኘቱን ማስረዳቱን የችሎቱ ታዳሚዎቹ ገልጸዋል፡፡ በመቀጠልም፣ ዓቃቤ ሕግ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ምርመራ መቀጠል ያለበት የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ሳይሆን፣ በፀረ ሽብርተኝነት ሕግ አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 28 መሠረት መሆኑን በማስረዳት ለምርመራ ጊዜ 28 ቀናት እንዲፈቀድለት መጠየቁንም አስረድተዋል፡፡
የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች በበኩላቸው ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ መርማሪ ቡድኑ ከዕለቱ ችሎት በፊት ሁለት ጊዜ አቅርቧቸዋል፡፡ ለፍርድ ቤቱም ያስረዳው ለጥርጣሬው ምክንያት የሆነው ተጠርጣሪዎቹ በተለያዩ ድረ ገጾች ላይ ኅብረተሰቡን ለአመፅ የሚያነሳሱ መጣጥፎችን መጻፋቸውን እንጂ ስለሽብር ያለው ነገር እንደሌለ ለፍርድ ቤቱ በማስረዳት፣ ፍርድ ቤቱ ከመዝገቡ ሊያረጋግጥ እንደሚችል መጠቆማቸውንም አስታውቀዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑም 15 ቀናት የምርመራ ተጨማሪ ጊዜ ጠይቆ ፍርድ ቤቱ በወቅቱ አሥር ቀናት ብቻ እንደሚበቃው በማመኑ አሥር ቀናት ብቻ ፈቅዶለት እንደነበር የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ ማስረዳታቸውን አክለዋል፡፡
ጠበቃ አመሐ መኰንን ተጠርጣሪዎቹን ለአንድ ቀንና ለአጭር ጊዜ አግኝተው ሲጠይቋቸው፣ መርማሪዎች በተደጋጋሚ የሚጠይቋቸው አንድ ዓይነትና ‹‹የዞን 9 አባል ነህ›› የሚል ብቻ መሆኑን ጠቅሰው፣ ስለሽብርተኝነት ምንም ዓይነት ጥያቄ ቀርቦላቸው እንደማያውቅ እንደነገሯቸው ለፍርድ ቤቱ አስረድተው፣ ‹‹መርማሪ ቡድኑ ምርመራዬን የምቀጥለው በሽብርተኝነት ሕጉ ነው፤›› ማለቱን መቃወማቸውን ገልጸዋል፡፡
ሥልጠና መውሰድን በሚመለከት ጠበቃ አመሐ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት ተጠርጣሪዎቹ ሥልጠና ወስደዋል የተባሉት ‹አርቲክል 19› እና ‹ፍሪደም ሐውስ› በሚባሉ ድርጅቶች መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ድርጅቶቹ በአሜሪካና በእንግሊዝ መንግሥታት ዕውቅና ያላቸው በሽብርተኝነት ያልተፈረጁ ሕጋዊ ድርጅቶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ላይ የሚሠሩ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያላቸው ድርጅቶች መሆናቸውን በማስረዳት፣ መርማሪ ቡድኑ ጉዳዩን ወደ ሽብር ለመውሰድ ከመናገር ያለፈ፣ ባለፈው ከመረመረውና ለፍርድ ቤቱ ካቀረበው ውጪ የጨመረው ስለሌለ ደንበኞቻቸው ዋስትና ተጠብቆላቸው ከእስር እንዲፈቱ አመልክተዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የሁለቱንም ወገን ማመልከቻ ካዳመጠ በኋላ፣ መርማሪ ቡድኑ የጠየቀውን የ28 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ በመፍቀድ የስድስቱን ተጠርጣሪዎች ችሎት አብቅቷል፡፡
እሑድ ግንቦት 10 ቀን 2006 ዓ.ም. የቀረቡት ደግሞ ጦማርያን አቤል ዋበላ፣ በፍቃዱ ኃይሉና ማህሌት ፋንታሁን ናቸው፡፡ ግንቦት 9 ቀን 2006 ዓ.ም. ቀርበው ለነበሩት ተጠርጣሪዎች መርማሪ ቡድኑ ያቀረበውን ተመሳሳይ የምርመራ ውጤትና ተመሳሳይ የ28 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቋል፡፡ የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃም ከላይ ለተጠቀሱት ተጠርጣሪዎች ያቀረቡትን መቃወሚያ ካቀረቡ በኋላ ፍርድ ቤቱ የራሱን ጥያቄ ለመርማሪ ቡድኑ አቅርቧል፡፡
ምን አዲስ ነገር በምርመራ መዝገባቸው ላይ እንዳያያዙ መርማሪ ቡድኑ እንዲያስረዳው ፍርድ ቤቱ ጥያቄ ሲያቀርብ፣ መርማሪ ቡድኑ የተጠርጣሪዎቹን የይለፍ ፈቃድ (ፓስ ወርድ) ተቀብሎ የተላላኩትን የኢሜል መልዕክት ሲፈትሽ፣ ከሽብርተኞች ጋር የተጻጻፉትን ማግኘቱን አስረድቷል፡፡ ከመዝገቡ ጋር ግኝቱን አያይዞ እንደሆነ እንዲገልጽ ፍርድ ቤቱ ሲጠይቀው፣ ገና አለማያያዙን በመግለጽ ላይ እያለ ፍርድ ቤቱ መዝገቡን ሲመለከት፣ ቀደም ብሎ ለጥርጣሬ ያበቃውን ከመጥቀሱ ሌላ ያለው ነገር አለመኖሩን በማየቱ፣ ወደ ሽብር ድርጊት የሚመራ ምክንያት ተጠቅሶ በመዝገቡ ላይ አለመቀመጡን በመግለጽ የተጠየቀውን 28 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ በግማሽ ቀንሶ የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ብቻ በመፍቀድ የዕለቱን ችሎት አጠናቋል፡፡