የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት አስተዳደር እና የግንባታ ፈቃድ ባለስልጣንየቀድሞው ስራ አስኪያጅ አቶ ቃሲም ፊጤና በሙስና ተጠርጥረው የተከሰሱት ሶስት ግብረ አበሮቻቸው ይከላከሉ ወይስ አይከላከሉ በሚለው ላይ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ተሰጠ።
ጉዳዩን እየተመለከተ የሚገኘው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ የወንጀል ችሎት ከከሳሽ የፌደራል ስነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አቃቤ ህግ ተጨማሪ የሰነድ ማስረጃ መቅረቡን ተከትሎ ከጠበቆች የተነሳውን ተቃውሞ በማገናዘብ ዛሬ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ይዞ ነበር።
በዚህም አቃቤ ህግ ያቀረበው ተጨማሪ የሰነድ ማስረጃ ክሱን ይበልጥ ያጠናክርልኛል ብሎ ሲያቀርብ የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው፥ የአቃቤ ህግ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች ቀርበው ከተጠናቀቁ በኋላ ተጨማሪ ማስረጃ አለ በመባሉ ነው ቅዋሜያቸውን ያሰሙት።
ችሎቱ ተጨማሪ የተባለውን ሰነድ መርምሮ በዛሬ ውሎው ማስረጃው የፍትህ ስርዓቱን ከማገዙ በቀር ጉዳት የለውም በማለት በተጨማሪነት ይዟል።
በክስ መዝገቡ ላይ አጠቃላይ የአቃቤ ህግ የሰውና የሰነድ ማስረጃ በመጠናቀቁ በተጨማሪ ሰነዱ ላይ አስተያየት ካለ እንዲቀርብ በማዘዝ፥ ተከሳሾች ይከላከሉ ወይስ አይከላከሉ በሚለው ጉዳይ ላይ ብይን በመስጠት ፍርድ ቤቱ ለመጋቢት 18፣ 2006 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።