ከ10 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ያለው ሐሰተኛ ሲ.ፒ.ኦ ያዘጋጀችው ግለሰብ በ6 ዓመት ከስድስት ወር እስራትና በገንዘብ ተቀጣች።
ተከሳሿ ወ/ሮ ፈዴላ ሃመዳኤል፣ በ2004 ዓ.ም የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በበጀት አመቱ ለሰራዊቱ የሚሆን የሱፍ ካፖርት ለመግዛት ባወጣው ጨረታ ላይ ነው ወንጀሉን የፈፀመችው።
የአቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው የአልፋ ጀነራል ትሬዲንገ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የተባለው ድርጅት ባለቤትና ስራ አስኪያጅ የሆነችው ተከሳሽ ፤ ኮሚሽኑ በ2004 ዓ.ም ባወጣው ውስን ጨረታ በመሳተፍ ፥ ድርጅቱ ለጠቅላላ ዋጋው 28 ሚሊዮን 961 ሺህ 600 ብር አሸናፊ ከሆነ በኋላ ውል ትፈፅማለች።
በመመሪያው መሰረት ፤ 10 በመቶ የመልካም አስተዳደር ስራ አፈፃፀም ዋስትና ፤ 30 በመቶ ደግሞ የቅድመ ዋስትና እንድታቆም ስትጠየቅ ፥
1ኛ) 8,688,480 (ስምንት ሚሊዮን ስድስት መቶ ሰማንያ ስምንት ሺህ አራት መቶ ሰማንያ ብር) ዋጋ ያለው ሐሰተኛ ሲ.ፒ.ኦ ከኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ እድገት ቅርንጫፍ ፤
2ኛ) 2,896,160 (ሁለት ሚሊዮን ስምንት መቶ ዘጠና ስድስት ሺህ አንድ መቶ ስልሳ ብር) ዋጋ ያለው ሀሰተኛ ሲ.ፒ.ኦ ከዳሽን ባንክ ሳሪስ ቅርንጫፍ እንደተሰጠ አስመስላ የሀሰት ሰነድ ለቅድመ ዋስትና ክፍያ እንዲያገለግል ለፖሊስ ኮሚሽኑ በማቅረቧ ነው ፤ አቃቤ ህግ ክሱን የመሰረተባት። በአጠቃላይ ተከሳሿ እንዚህን ሁለት ሐሰተኛ የሲ.ፒ.ኦ ሰነዶችን አዘጋጅታ ለኮሚሽኑ የቅድመ ክፍያ 8,684,400 (ስምንት ሚሊዮን ስድስት መቶ ሰማንያ አራት ሺህ አራት መቶ ብር) የቅድመ ክፍያ በመውሰድ በፈፀመችው መንግስታዊ ሰነዶችን በሀሰት አስመስሎ ማዘጋጀትና በእነዚህ ሰነዶች መገልገል የሙስና ወንጀል ተከሳ ጥፋተኛ ተብላለች።
መዝገቡን ሲመረምር የቆየው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ ወንጀል ችሎት ፥ የፈፀመችው ከፍተኛ ወንጀል በዘጠኝ አመት ፅኑ እስራት የሚያስቀጣት ቢሆንም ተከሳሿ የስድስት ልጆች እናት ነኝ ፣ ብዙ ሰራተኞችን ቀጥሬ በስሬ አሰራለሁ ፣ በወንጀሉም ተፀፅቻለሁ እንዲሁም የልብና የአስም በሽተኛ ነኝ በማለቷና ከዚህ በፊት ምንም የወንጀል ሪከርድ ስላልነበራት፤ ያቀረበችው የቅጣት ማቅለያ ተቀባይነት አግኝቶ በስድስት አመት ከስድስት ወር እስራትና በ10ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንድትቀጣ ተወስኖባታል።