የፍትሕ ሥርዓቱ ከሃገሪቱ ኢኮኖሚ እኩል ሊያድግ ይገባል አሉ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ። ትናንት ሃገር አቀፍ የፍትህ ዘርፍ የመልካም አስተዳደር መድረክ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት አዳራሽ ሲጀመር ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት።
በመድረኩ ያለፉት ሶስት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን አመታት የፍትህ ስርዓቱ ያለበት ደረጃ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።
የኢትዮጵያ የፍትህ ስርአት የሀገሪቱን ልማት ምን ያክል አግዟል ፤ መልካም አስተዳደርንስ ከማምጣት አንጻር ምን ያክል ሚና ተጫውቷል የሚለው ጉዳይም ተገምግሟል። የኢፌደሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ፥ የፍትህ ስርአቱ ያሉበትን ችግሮች ለማቃለል ከአመታት በፊት የማሻሻያ ስርአት ተነድፎ ፤ መንግስትም ዘርፉን ለማሻሻል በርካታ ስራዎችን ማከናወኑን ተናግረዋል።
እያደገ ያለው ምጣኔ ሀብት በሀገሪቱ ያሉ የእርስ በርስ ግንኙነቶችን ማወሳሰቡ የማይቀር በመሆኑም ፤ ይህን ፍላጎት የሚሸከም የፍትህ ስርአት መገንባትም የግድ ነው ብለዋል።
ከዚህ አንጻር ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል የመጣ ቢሆንም የህዝቡ ቅሬታዎች ግን አሁንም አሉ ፤ በፍትህ ስርአቱ ላይ ቀድሞ የነበሩ ጉድለቶችን ለመፍታት 54 ፕሮጀክቶች ተቀርፀው 24 ያህሉ በተለያዩ የፍትህ አካላት ተግባራዊ እየተደረጉ ይገኛሉ ነው ያሉት።
በሀገሪቱ መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አንጻር የዳኞች ፣ አቃብያነ ህግ እንዲሁም የፖሊሶች የዘርፉ አስተዋጽኦ እና የፍትሃ ብሄር አስተዳደር ውጤታማነት ለግምገማ የቀረቡ መስፈርቶች ናቸው።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ተገኔ ጌታነህ በበኩላቸው ፥ ከአመታዊ በጀቷ 60 በመቶውን ለግዥ የምታወጣው ኢትዮጵያ ውሎች በተገቢው መንገድ የማይፈጸሙ በመሆኑ ችግሮች ሲከሰቱ ለተጨማሪ ወጪ እየተዳረገች መሆኑን ገልፀዋል።
በየመስሪያ ቤቶች የሚፈጸሙ ግዥዎች ተገቢውን የውል ስርአት ተከትለው መፈጸማቸውን ማረጋገጥ አለመቻሉ እና በፍትህ ስርአቱ ላይ ብልሹ አሰራሮችን ለማስቀረት በቂ አሰራር አለመኖሩ ህዝቡ በዘርፉ ላይ ያለውን እምነት እየጎዳው ነውም ብለዋል።
የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች እጥረት ፥ የፍትህ ዘርፉ በርካታ የሰው ፍልሰት እንዲያጋጥመው ምክንያት ሆኗል ፤ ይህም ለፍትህ ስርአቱ በቂ የሰው ሀይል እንዳይኖር አድርጓል ነው የተባለው። በውይይቱ በዳኞች ፣ በአቃቢ ህጎችና በፖሊሶች በኩል የሚታዩ ድክመቶችም ተነስተዋል ።
የሚሰጡ ውሳኔዎች ከ2004 ይልቅ የ2005 በልጦ መገኘቱ ፤ የመዝገብ መጨናነቅንም መቀነስ መቻሉ ፤ መዝገብን የማጣራት አቅምም መጨመሩ ፤ እንዲሁም የህዝብንና የመንግስትን ጥቅም በመንካት ለተፈጸሙ ወንጀሎች አቃቤ ህግ የሰራው የመዝገብ ማጣራት እና የማስፈረድ አቅም መልካም ሆኖ ተገኝቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ፥ ያሉ ስኬቶች እንዳሉ ሆነው ጉድለትን ማሟላት ሰፊ ቦታ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
በአጠቃላይ የፍትህ ስርአቱ ላይ ያሉ ችግሮች እንዴት ይፈታሉ ለሚለውም ዛሬ አንድ እቅድ ይቀርባል። (ዘገባው የሬዲዮ ፋና ነው)