በነአቡበከር መሀመድ የክስ መዝገብ የመከላከያ ማስረጃ ለመከታተል የተያዘው ቀጠሮ ወደ መጋቢት 20 ተሸጋገረ። 18 ተከሳሾች ያሉበት ይህ መዝገብ ዛሬ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ የወንጀል ችሎት ቃሊቲ ነበር ሊታይ ቀጠሮ ተይዞ የነበረው።
ተከሳሾቹ በጠበቆቻቸው አማካኝነት ከ400 በላይ የሚሆኑ የመከላከያ ማስረጃዎችን ማዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።
ከሳሽ የፌደራል አቃቢህግ አቀራረባቸውን አስመልክቶ ለፍርድ ቤቱ ተቃውሞ ያቀረበ ሲሆን ፥ ማን ለማን እንደሚመሰክር እና ጭብጡን እንዲያቀርቡ ጠይቋል።
ግራ ቀኙን የመረመረው ፍርድ ቤቱ የአቃቢህግን አቤቱታ በመቀበል ጭብጥ አስይዙ ብሎ ሲበይን ፥ የተከሳሽ ጠበቆች ይህን ለማድረግ የአንድ ወር ጊዜ ጠይቀዋል።
ችሎቱ የራሱን የጊዜ ሰሌዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት ፥ በብይኑ መሰረት መዝገቡን ለመመልከት ለመጋቢት 20 2006 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።